የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸምና የተማሪዎች ውጤት ትንተና የእውቅና እና ሽልማት ፕሮግራም አካሄደ።

መጋቢት 13, 2017      Admin
በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተ.ወ.ማ ፕሬዚዳንት አቶ ሃሰን ሺፋን ጨምሮ የክ/ከተማ ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክ/ከተማ የመሠረታዊ መምህራን ማህበር አባላት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ ግርማ በንግግራቸው የዛሬው የትምህርት ጉባዔ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በክፍል ፈተና እንዲሁም በሞዴል ፈተና የተማሪዎቻችን ውጤት እንደ ት/ቤት ብሎም እንደ ክ/ከተማ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት እና በቀጣይ ለሚሰጠው የከተማ እና ሃገር አቀፍ ፈተናዎች ምን ማድረግ አለብን የሚለውን እንድንወያይ ነው ብለዋል። በጽ/ቤቱ የቡድኖች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ገዳ ሞሲሳ በበኩላቸው በተለይ በከተማ ደረጃ በተደረገው ምዘና ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ እና የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች ልዩ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። አያይዘውም በውጤት ትንተናው ላይ የተገለጹ ትኩረት የሚሹ የት/ዓይነቶች ስልቶችን ቀይሰን መስራት ይኖርብናል ብለዋል። አቶ አቡበከር አህመድ በጽ/ቤቱ የቡድኖች አስተባባሪ የሆኑት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በክ/ከተማ እንዲሁም በት/ቤት ደረጃ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰው በተለይ ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው ት/ቤቶች ትልቅ ስራ ይጠብቃችኋል ብለዋል። የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቡድን መሪ አቶ መንግሰቱ ኦሳቦ እና የፈተና እና መረጃ ትንተና ባለሙያ የሆኑት አቶ ግርማ ወንድሙ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ትምህርት መርሃ ግብር የተማሪዎች ውጤት ትንተና አቅርበዋል። ውጤት ትንተናው በክ/ከተማ ደረጃ በመንግሥት እና በግል ት/ቤቶች፣ በቀን እና በማታ፣ በክፍል ደረጃ እና በት/ቤት ደረጃ ተተንትኖ ቀርቧል። በተጨማሪም ከ2015 ዓ.ም - 2017 ዓ.ም ያለውን የተማሪዎች ውጤት በንጽጽር ቀርቧል። በቀረበውም ውጤት ትንተና ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በመጨረሻም በ2017 ዓ.ም በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በተደረገ የቁልፍ ውጤት አመላካች [KPI] እና የሪፎርም ስራዎች ምዘና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች እውቅናና ሽልማት ተሠጥቷል።

ተያያዥ መረጃዎች