የልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ዓመታዊውን የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ አካሄደ።

ሚያዚያ 2, 2017      Admin
በመርሀ ግብሩ ላይ የጽህፈት ቤቱ አመራሮችና ባለሙያዎችን ጨምሮ መምህራን፣ ወላጆች፣ ርዕሳነ መምህራን እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ባለሙያዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ ግርማ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በትምህርት ሴክተሩ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በ2017ዓ.ም በክፍለ ከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተሰሩ ከ30 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች መካከል በክፍለ ከተማው የጥናትና ምርምር ኮሚቴዎች የተለዩ 4 ስራዎች በዛሬው ኮንፍረንስ እንዲቀርቡ መደረጉን አመላክተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዮሀንስ ተስፋዬ(ዶክተር) በበኩላቸው የልደታ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት በስሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በማስተባበር በዚህ መልኩ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመምህራን እንዲቀርብ ማድረጉ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ጠቁመው የጥናትና ምርምር ስራዎቹ ለሚፈለገው አላማ እንዲውሉ በቢሮው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል። በኮንፍረንሱ በመካኒሳ አካባቢ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 7ኛ ክፍል አፋን ኦሮሞ ቋንቋን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የሚማሩ 30 ተማሪዎችን የንባብ ክህሎት ማሻሻልን መሰረት አድርጎ በትምህርት ቤቱ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ መምህር የተሰራ ጥናት፣ የእውቀት ብርሀን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የክፍል ውስጥ ተሳትፎ ለማሻሻል በትምህርት ቤቱ መምህር የተዘጋጀ ጥናት፣ የብስራተ ገብርኤል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ መምህራን በቤተ ሙከራ የተደገፈ የትምህርት አገልግሎት በምን መልኩ ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ ለማረጋገጥ በትምህርት ቤቱ መምህር የተሰራ የጥናትና ምርምር ስራ እንዲሁም በመዝገበ ብርሀን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን የእንግሊዘኛ ቋንቋ የክፍል ውስጥ የተግባቦት ክህሎት እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል በትምህርት ቤቱ 2 መምህራን የተሰራ የጥናትና ምርምር ስራ ቀርቦ ዕውቅና ተሰጥቷል።

ተያያዥ መረጃዎች