የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት "በፈጠራ ስራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሃገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የሳይንስና ፈጠራ አውደ ርዕይ በድምቀት አካሄደ።

ሚያዚያ 14, 2017      Admin
በአውደ ርዕዩ ላይ የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ሃፍቱ ብርሃኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተ.ወ.ማ ፕሬዚዳንት አቶ ሃሰን ሺፋ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና ከልደታ ክ/ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል። የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ሃፍቱ ብርሃኑ በንግግራቸው በየዓመቱ የሚደረገው የሳይንስና ፈጠራ አውደ ርዕይ መምህራን እና ተማሪዎች ቴክኖሎጂን እንዲለማመዱ፣ እንዲፈጥሩና እንዲያሸጋግሩ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቅሰው ሃሳብ የሚያጎለብቱ መምህራን እና ተማሪዎችን ልናከብራቸው ይገባል ብለዋል። አቶ ሃፍቱ አያይዘውም በየዓመቱ የሚደረገው የሳይንስና ፈጠራ ስራን ጨምሮ የተማሪዎች የonline ፈተና በቴክኖሎጂ የታገዘ እና የተደገፈ እንዲሆን ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ግንባር ቀደም ስራዎችን እየሰራ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ ግርማ በበኩላቸው የዛሬው የሳይንስና ፈጠራ አውደ ርዕይ በዓመቱ ውስጥ ተማሪዎች በቲዮሪ የተማሩትን መምህራን ደግሞ ያስተማሩት በተግባር የሚያሳዩበት ነው ያሉ ሲሆን የሳይንስና ፈጠራ ስራ ዋና ዓላማው ችግር መፍታት እንደመሆኑ በዛሬው አውደ ርዕይ አዳዲስና ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን እንጠብቃለን ብለዋል። አቶ አሠፋ አያይዘውም የተሻለ መፍትሔ ይዞ የመጣ መምህር እና ተማሪ በክ/ከተማ ብቻ ሳይሆን በከተማ ደረጃ ጭምር አሸናፊ የመሆን እድሉ ሠፊ መሆኑን ገልጸዋል። በዕለቱ የተገኙት የክብር እንግዶች በመምህራንና በተማሪዎች የተሠሩ የፈጠራ ስራዎችን እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል። ባዩትም የፈጠራ ስራዎች መደሠታቸውን ገልጸዋል። በመጨረሻም የተሻለ የፈጠራ ስራ ላቀረቡ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የተሻለ ሽብርቅ ላሳዩ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል።

ተያያዥ መረጃዎች