የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ከልደታና አዲስ ከተማ ክ/ከተማ የትምህርት ጥራትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በክፍለ ከተማው ለሚገኙ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ባለሙያዎች በትምህርት ቤት መሻሻል ማእቀፍና የኢንስፔክሽን ማእቀፍ አተገባበር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡

ሚያዚያ 8, 2017      Admin
በትምህርት ጽ/ቤት የት/ቤት መሻሻልና ግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ጉልላት የት/ቤት መሻሻል ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ አላማዎች፣ የት/ቤት መሻሻል አብይ እና ንዑስ ርዕሰ ጉዳዮች እንዲሁም የተሻሻሉ ስታንዳርዶችና አመላካቾች እና ሌሎች ርዕሶች ላይ በዝርዝር ግንዛቤ የፈጠሩ ሲሆን በተለይ በቀጣይ የሚዘጋጀውን የ3 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ከተቀመጡ የስታንዳርድ ደረጃዎች አንጻር እንዴት መታቀድ እንዳለበት በሰፊው ገለጻ አድርገው ተሳታፊዎች በቡድን እንዲለማመዱ አድርገዋል። የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ ግርማ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት የት/ቤት መሻሻል ስትራቴጂክ እቅድ ለት/ቤት ዋና እና ቁልፍ መሆኑን ገልጸው እቅዱን በአግባቡ ለማቀድ የተሻሻሉ ስታንዳርዶች እና አመላካቾችን ማወቅና መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ርዕሳነ መምህራን ስልጠናውን በትኩረት በመከታተል፣ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ት/ቤቶችን ከግብዓት፣ ከሂደት እና ከውጤት አንጻር የተሻለ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። አቶ አንዋር አብዲ የባለስልጣኑ የልደታና አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው የት/ቤት መሻሻል ማእቀፍና የኢንስፔክሽን ማእቀፍ በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ከተደረገና እንደ አዲስ ከተተገበረ በኋላ ወደታች በማውረድ ግንዛቤ መሰጠቱ በት/ቤት መሻሻልና ኢንስፔክሽን ማእቀፍ ላይ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። አያይዘውም የተቋማትን ደረጃ ለመግለጽ እና ለማወቅ በተጨማሪም እቅድ በማቀድ ደረጃን ማሻሻል እና የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ተያያዥ መረጃዎች