የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉ የመንግስት ት/ቤቶች በአጠቃላይ የማኔጅመንት አወቃቀር፣ የፋይናንስ ስርዓት እንዲሁም የሠው ኃይል አስተዳደር ዙሪያ በከተማ ደረጃ የተደረገ ጥናት ርዕሳነ መምህራን፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ባለሙያዎች በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ተደረገ።

ሚያዚያ 24, 2017      Admin
ጥናቱን የትምህርት ጽ/ቤት የቡድኖች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ገዳ ሞሲሳ ያቀረቡ ሲሆን ጥናቱ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም እስከ የካቲት ወር 2017 ዓ.ም በመንግስት ት/ቤቶች ያለውን የፋይናንስ፣ የንብረት፣ የግዢ እንዲሁም የክፍያ ስርዓቱን ያካተተ ሲሆን ት/ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ ህጋዊ ስርዓቱን በተከተለ መልኩ እየተገበሩ አለመሆኑ፣ ለትምህርት ለትውልድ የገቢ ማሠባሰቢያ ህጋዊ ደረሠኝ አለመኖር፣ የማኔጅመንት አወቃቀር ላይ ክፍተት መኖሩ፣ የውስጥ ገቢ ምንጭ አሠባሠብ ላይ ክፍተት መኖሩ፣ የማታ ትምህርት የክፍያ አፈጻጸም፣ ወተመህ ራሱን የቻለ አካውንት አለመኖር...... በጥናቱ ተካቶ ቀርቧል። መረጃው ከተማሪዎች፣ ከመምህራን እና ከአስ/ሠራተኞች የተሠበሠበ መሆኑ በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል። የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ ግርማ እንደተናገሩት አሠራርና መመሪያን ተከትሎ መሠራት የሚገባቸው ስራዎች በግዴለሽነት ወይም መመሪያ ጠንቅቆ ባለመረዳት ምክንያት በፋይናንስ፣ በግዢ ስርዓት እንዲሁም በተማሪዎች ምገባ ዙሪያ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ገልጸው በአስቸኳይ ት/ቤቶች ክፍተቶችን ገምግመው ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን ተጠያቂ በማድረግ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል። በጽ/ቤቱ የቡድኖች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ገዳ ሞሲሳ በበኩላቸው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስህተት ውስጥ የገቡ አካላት መኖራቸውን ገልጸው በአስቸኳይ የማስተካከል ስራ መሠራት እንዳለበት እንዲሁም ለተቀመጥንበት ቦታ በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት መስራት እንዳለብን አፅንዖት ሠጥተው ተናግረዋል። በተመሳሳይ በጽ/ቤቱ የቡድኖች አስተባባሪ የሆኑት አቶ አቡበከር አህመድ እንዳሉት በከተማ ደረጃ ተጠንቶ የቀረበው ጥናት በተለይ ከምገባ ጋር ተያይዞ የተነሱ ክፍተቶች በክ/ከተማ ደረጃ ባካሄድነው ክትትልና ድጋፍ የተገኘ ግኝት በመሆኑ በትክክልም ክፍተት እንዳለ በደንብ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ግልጸኝነት አለመኖር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ተያያዥ መረጃዎች